በወረዳችን ኧዣ ስር ሰደው የሚገኙ በርካታ ችግሮችን በመለየት እንዴት መቅረፍ ይቻላል በሚለው ላይ ከበርካታ ተወላጆች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ከተደረጉ በሗላ የበጎ አድራጎት ድርጅት መመስረት እንደሚሻል ታመነበት::
በዋናነት የበጎ አድራጎት ድርጅት የተመረጠበት ምክንያት:
- ችግሮቹ የበዙ በመሆናቸው ባለን ውስን አቅም ብዙሃኑን የሚያሳትፍና ብዙ ዓይነት ስራዎችን ጎን ለጎን መስራት የሚያስችል አደረጃጀት በመፈለግ:
- እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ተወላጆች ተሳታፊ እንዲሆኑ : የዓባልነት ክፍያ በመፈፀም ገቢ እዲያስገኙና ቀጣይነት እንዲያረጋግጡ በማሰብ
- ባለ ሀብቶች በገንዘብና ሙያተኞች በየሙያቸው በመደራጀት ችግሮችን ለመፍታት ወደ ሗላ እንደማይሉ ተስፋ በማድረግ
- ከትላልቅ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች : ከምርምርና የመንግስት ተቋሟት የዕውቀትና የገንዘብ ድጋፍ ሊገኝ እንደሚችል በማመን ነበር::
በዚሁ መሠረት ጋበር የበጎ አድራጎት ድርጅት ነሓሴ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በመዝገብ ቁጥር 6365 በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዘገቦ ሕጋዊ ሰውነት አገኘ::
ጋበር በአንድ ዓመት ተኩል እድሜው ከኧዣ ወረዳ አስተዳደር ጋር በመተባበር ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት:
- በአዲስ አበባ ነዋሪ ከሆኑ ተወላጆች ጋር በጣም ብዙ የግንዛቤ ማስጨበጫና የገቢ ማሰባሰብያ ስብሰባዎችን አካሄዷል : በማካሄድም ላይ ይገኛል::
- በወረዳችን ችግሮች ላይ ያተኮረ ውይይት ከወረዳውና ከአገና ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ጋር አድርጓል:: ችግሮቹን እጅ ለእጅ ተያይዘን ለመፍታት ቁርጠኛነት መኖሩን አረጋገጠ::
- የጋበር ቢሮና የበላይ አመራርን (አንድ ዋና ስራ አስኪያጅ : አንድ የአስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊና አንድ የሞኒተሪንግና መምርያ ኃላፊ) አዋቀረ::
- በትምህርት ላይ ያሉትን ችግሮች ለመለየት በከፍተኛ ባለሙያ በመታገዝ ተማሪዎችን : መምህራንን : የትምህርት አመራርን : የወላጅ ኮሚቴን ያካተተ ሰፊ ጥናት አካሄዷል::
- ሁለት ጊዜ ከአገና ከተማ አስተዳደርና ከ28ቱ የገበሬ ማህበራት ተወካዮች ጋር በወረዳችን ስር ሠደው በሚገኙ ችግሮችና መፍቻ ዘዴዎቻቸው ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት አካሄዷል::
- በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ የኧዣ ተወላጆች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ጋበር ሠፖርት ግሩፕ ኖርዝ አሜሪካ የተሠኘ ህጋዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተቋቁሞ አባላት በማሰባሰብና የአባልነት ክፍያ በመሠብሰብ ላይ ይገኛል:: በአውሮፓ ከሚኖሩ ተወላጆች ጋርም ተመሳሳይ አደረጃጀት ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው::
- በኣርቲስት አብርሃም ወልዴ እና በባለቤቱ ወ/ሮ ማክዳ ኃ/ሚካኤል በተደረገለዠት የብር 250 ሺህ ልገሳ 450 የብርድልብሶች ገዝቶ ለወገኖቻችን አድሏል::
- የጋበር ቴሌግራም ተከታዮች ቁጥር ለማብዛትና ለተማሪዎች መጻህፍት ማሳተሚያ ገንዘብ ለማሰባሰብ በተደረገ ከፍተኛ ጥረት በርካታ ተከታዮች ማፍራትና በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ከሚኖሩ ተወላጆችና ቸር ኢትዮጵያውያን በሚሊዮኖች ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል::
*በወረዳው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ላሉ ሁሉም ተማሪዎች ለ6 የትምህርት ዓይነቶች አንድ መጽሃፍ ለ5 ተማሪዎች መጠቀምያ እንዲሆን አሳትሞ አድሏል::
- በወረዳው ለሚገኙ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በርካታ የማጣቀሻ መጽሃፍት በእርዳታና በግዥ አግኝቶ አከፋፍሏል
- በወረዳው ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ሁሉም ሴት ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የሚያገለግል የንጽህና መጠበቂያ አስመርቶ አከፋፍሏል::
- በወረዳው ለሚገኙ 2ኛ ደረጃ እና ለአገና ኢንደስትርያል ኮሌጅ ተማሪዎች በባለሙያ የተዘጋጀ የጥናት ሠነድ መሠረት በማድረግ በስነምግባርና በእውቀት የሚበለጽጉበትን ምክርና ውይይት በየትምህርት ቤታቸው በመገኘት አካሄዷል::
- በአንድ ቀን ከመላው የኧዧ ነዋሪዎች ጋር አገር ቤት በየገበሬ ማህበራቸው በመገኘት በችግሮችና መፍቻ ዘዴዎች ላይ የግማሽ ቀን ውይይት አካሄዷል:: በውይይቱም የኧዣን መሠረታዊ ችግሮች ከህብረተሰቡ በግለጽ የተነሱ ሲሆን ለመፍትሄውም ህብረተሰቡን የሚያስተባብሩ : በኣርኣያነታቸው እምነት ያተረፉ ዓባላት ያካተተ ኮሚቴ በሁሉም የቀበሌ ገበሬ ማህበር እንዲቋቋም ተወስናል:: የኮሚቴ ኣባላት ምርጫ የተጠናቀቀ ሲሆን ኃላፊነታቸውን በተመለከተም በቅርቡ የጋራ ውይይት ይካሄዳል::
- የወረዳችንን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉና ብሎም ከፍ የሚያደርጉ በቦርድ ዓባላት የሚመሩ 9 ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ስራ በመግባት ላይ ይገኛሉ::
- የ2015 የትምህርት ዘመን አገር አቀፍ ፈተና ከተፈተኑ ተማሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ በቀጥታ ለዩኒቨርስቲና ለሪሜዳል ትምህርት ያለፉትን በትምህርታቸው እንዲበረቱ መክሯል : በባለሙያ የአጠናን ዘዴዎችን አስረድቷል:: የማበረታቻ ስጦታም አድርጓል:: የተቀሩት ተማሪዎችም አገና ኢንዱስትርያል ኮሌጅ ገብተው ስልጠና እንዲወስዱ የቴክኒክ ሙያን ዘርፈ ብዙ ጥቅም አስረድቷል:: ወጣቱ በተለያዩ ሙያዎች በመሳተፍ በአካባቢዬም ሠረቼ ያልፍልኛል የሚል ስሜት እንዲያዳብር ሰፊ ቅስቀሳ ተደርጓል::
- በውኃና መስኖ ላይ ጥናት የሚያደርግ የከፍተኛ ሙያተኞች ቡድን ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል::
- በኧዣና በቤተሰብ ስም የተቋቋሙ ዕድሮች በርካታ ህዝብ ያቀፉ ስለሆኑ ጋበርን የሚደግፉበት ዘዴ ለመቀየስ እድሮችን በተመለከተ አኩሪ ተግባር ከፈፀመው የኧዣ ዕድሮች ህብረት ቢዝነስ አክስዮን ማህበር የቦርድ አመራር ጋር ገንቢ ውይይት አካሄዷል::
ክብርና ምስጋና በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችሁን ለመርዳት የአቅማችሁን ለምታደርጉ ሁሉ ይሁን::
የጋበር ኣባል ይሁኑ : በገንዘብዎና በሙያዎ ጋበርን በመርዳት እዳዎን ይከፊሉ ::
አቶ ኮሬ ባዌ፤ የጋበር በጎ አድራጎት ድርጅት ሊቀመንበር