Gaber latest news

“ጋበር ” የበጎ አድራጎት ማህበር በዚህ ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎች ለያንዳንዳቸው ከ15 ሺህ ብር ጀምሮ በየደረጃው የገንዘብ ድጋፍ አደረገ ።
ማህበሩ በህዳር 22፤2016 ዓ።ም ከእዣ ወረዳ አስተዳደር ጋር በመተባበር የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች የዕውቀትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል ።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማርያም እንደገለፁት ጋበር በጎ አድራጎት ማህበር እያከናውናቸው ያሉት ተግባራቶች እንደ እዣ ወረዳ ብሎም እንደ ጉራጌ ዞን የትምህርት ውጤት ስብራትን ለማካካስ ትልቅ አቅም የሚፈጥር በእውቀቱ የዳበረ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ለማፍራት የሚያስችል አርዕያ ያለው ተግባር ነው ።
ማህበሩ ከሁሉም በላይ ለየት የሚያደርገው የማህበረሰቡ አስተሳሰብ ለመቀየር የጀመረው ተግባር ነው ያሉት ሀላፊው ከአርሶአደር ጀምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማወያየት በትምህርት በጤና ፡ በግብርናና በሌሎችም ዘርፎች እንዴት መለወጥ እንደሚቻልና ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ ተሞክሮዎችንም ጭምር በተግባር በማሳየት የጀመረው ስራ የሚበረታታ ነውም ብለዋል።
ከብዙ ልማቶች ሁሉ ልማት የሚባለው የሰው ልጅ አእምሮ ማልማት መሆኑን ማህበሩ በጥልቀት ተገንዝቦአል ያሉት አቶ መብራቴ በተለይም የተማሪዎች ውጤት ለማሳደግ መፅሀፍቶችን ከመግዛትና ሌሎች በዘርፉ ያሉት ማነቆዎች ለመፍታት እያደረገው ያለው ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደ ዞኑ እውቅና የሚሰጠውና ተሞክሮ የሚሆንም ጭምር በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋልም ብለዋል።
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በዚህም እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በሀገራችን ብሎም በወረዳችን የትምህርት ሽፋን ላይ በስፋት ቢሰራም የጥራቱ ጉዳይ በሽፋኑ ልክ ትኩረት ተሰጥቶት ባለመሄዱ ከፍተኛ የሆነ የትምህርት ውጤት ስብራት አጋጥሞናል ብለዋል።
በመሆኑም ወረዳችን የዚህ ተፅኖ ተጋሪ ሆኗል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ለዚህም ማሳያ በ2015 ዓም ፈተና ከወሰዱት 448 ተማሪዎች መካከል 28ቶቹ ወደ ዩኒቨርስቲ በቀጥታ የሚገቡ ሲሆን 116 ተማሪዎች ደግሞ የማስተካከያ ትምህርት የሚወስዱ መሆኑንኑንና ሌሎች 330 ወደ ቴክኒክና ሙያ የሚገቡ ናቸው ብለዋል።
የገጠመንን የውጤት ስብራትና የትምህርት ቤት መሰረተ ልማት ጉለት ለሟሟላት በተለይም ጋበር የበጎ አድራጎት ማህበር እያደረገው ያለው ከፍተኛ የሆነ ሁለንተናዊ ድጋፍ በወረዳው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
የእዣ ወዳ ም/አስተዳዳሪና የትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ በበኩላቸው በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፡ ማህበራዊ ፡ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርግ በስነ ምግባሩ የታነፀ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆን በርካታ ቀሪ ስራዎች መስራት እንዳለብን አመላካች ነው ብለዋል።
ሀላፊው አክለውም ኩረጃን የሚጠየፍ በራሱ የሚተማመን ዜጋ ከማፍራት አኳያ ሰፋፊ ጉለቶች መኖራቸውን በ2014 እና በ2015 የተሰጠው ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ጉልህ ማሳያ ነው ።
እንደ ወረዳው ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎች እና ወደ ቴክኒክና ሙያ ገብተው በአጭር ግዜ እራሳቸውና ሀገራቸው ለመጥቀም ሰፊ እድል ያላቸው ተማሪዎች መልካም ቀሪ ጊዜ እመኛለሁ ያሉት አቶ ተጠምቀ በቀጣይ የትምህርት ባለድርሻ አካላትም በትምህርት ዘርፉ ያሉት ማነቆዎች በቁርጠኝነትና በባለቤትነት በመስራት የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።
የጋበር በጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኮሬ ባዌ በበኩላቸው ድርጅቱ በዋናነት አላማ አድርጎ የተቋቋመው በእዣ ወረዳ ያሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን መንግስት ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት የአካባቢው ህብረተሰብ በማስተባበር የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችል ነው ብለዋል።
በተለይም ድርጅቱ በትምህርት ዘርፍ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት መጽሀፍ ገዝቶ ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ በዚህ ዙር በ2015 ዓም ሀገር አቀፍ ፈተና ውስደው ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡና በተለያየ መልኩ የማበረታቻ ሽልማት ያዘጋጀ ሲሆን ቀሪዎች ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ገብተው እንዲማሩ የማስገንዘብ ስራ ለመስራት ነው ብለዋል።

ተማሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ጋበር የበጎ አድራጎት ድርጅት ባደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ጠቁመው ይህም ድጋፍ ይበልጥ ውጤታማ ሆነን ለራሳችን ፡ ለአካባቢያችን ብሎም ለሀገራችን እንድጠቅም እገዛ የሚያደርግልን የሞራል ስንቅ ነው ብለዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።